ዘፍጥረት 26:16-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. አቢሜሌክም ይስሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው።

17. ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ።

18. ይስሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኑአቸውን የውሃ ጒድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው።

19. የይስሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጒድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ።

20. የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይስሐቅ ያን የውሃ ጒድጓድ ኤሴቅ ብሎ ጠራው፤ በጒድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና።

21. አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጒድጓዱን ስጥና ብሎ ጠራው።

22. ይስሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጒድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጒድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት ብሎ ጠራው።

23. ከዚያም ይስሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ።

24. በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም) ነኝ፤ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው።

25. ይስሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ።

26. አቢሜሌክም ከአማካሪው ከአዘኮትና ከሰራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ከጌራራ ተነሥቶ ይስሐቅ ወዳለበት ስፍራ መጣ።

27. ይስሐቅም፣ “ጠልታችሁኝ ካባረራችሁኝ በኋላ፣ አሁን ደግሞ ለምን መጣችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።

28. እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአንተ ጋር መሆኑን በግልጽ ተረድተናል፤ ስለዚህም፣ ‘በመሐላ የጸና ውል በመካከላችን መኖር አለበት’ አልን፤ ይህም በእኛና በአንተ መካካል የሚጸናውል ነው፤ አሁንም ከአንተ ጋር ስምምነት እናድርግ፤

29. አንተን እንዳልጐዳንህ፣ ነገር ግን በጎነትን እንዳሳየንህና በሰላም እንደ ሸኘንህ ሁሉ፣ አንተም ክፉ እንዳታደርግብን በመካከላችን ውል ይደረግ፤ አንተን እንደሆን መቼም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባርኮሃል።”

30. ይስሐቅም ድግስ ደግሶ፣ አበላቸው፤ አጠጣቸው።

31. በማግስቱም በማለዳ ተነሥተው፣ በመካከላቸው መሐላ ፈጸሙ። ይስሐቅም አሰናበታቸው፤ እነርሱም በሰላም ሄዱ።

32. በዚያኑ ዕለት፣ የይስሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለ ቈፈሩት የውሃ ጒድጓድ ነገሩት፤ “ውሃ እኮ አገኘን!” አሉት።

ዘፍጥረት 26