ዘፍጥረት 15:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህም በኋላ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤“አብራም ሆይ፤ አትፍራ፤እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ታላቅ ዋጋህም እኔው ነኝ።

2. አብራምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላክ ሆይ፤ ያለ ልጅ የቀረሁ ስለ ሆንሁ፣ የቤቴ ወራሽ የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር ነው፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” አለው።

3. “አንተ ልጆች ስላልሰጠኸኝ፣ ከቤቴ አገልጋይ አንዱ ወራሼ መሆኑ አይቀርም።”

4. በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፤ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል።”

5. ወደ ውጪም አውጥቶ፣ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቊጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቊጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል” አለው።

6. አብራም እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት።

ዘፍጥረት 15