3. እስራኤላውያንም እነርሱን እንዲህ አሏቸው፣ “በሥጋ መቀቀያው ምንቸት ዙሪያ ተቀምጠን የፈለግነውን ያህል ምግብ መመገብ በምንችልበት በግብፅ ሳለን፣ ምነው በእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እናንተ ግን ይህ ሁሉ ጉባኤ በራብ እንዲያልቅ ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን” አሏቸው።
4. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ። ሕዝቡም በየቀኑ እየወጡ ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰበስቡ፤ በዚህም ትእዛዛቴን ይጠብቁ እንደሆነ እፈትናቸዋለሁ።
5. በስድስተኛው ቀን በሌሎቹ ዕለታት ከሚሰበስቡት እጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።
6. ስለዚህ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ እንዲህ አሉ፤ “ከግብፅ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኑን በዛሬይቱ ምሽት ታውቃላችሁ።
7. በእርሱ ላይ ያሰማችሁትን ማጒረምረም ሰምቷልና በማለዳ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ክብር ታያላችሁ፤ ለመሆኑ በእኛስ ላይ የምታጒረመርሙት እኛ ምንድን ነንና ነው?” አሏቸው።
8. ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በእርሱ ላይ ማጒረምረማችሁን ሰምቶአልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጒረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ ነው እንጂ” አላቸው።
9. ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ‘ማጒረምረማችሁን እርሱ ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ቅረቡ’ ብለህ ለመላው የእስራኤል ማኅበር ተናገር” አለው።
10. አሮንም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ሲናገር ሳለ ወደ ምድረ በዳው ተመለከቱ፤ በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር በደመናው ላይ ተገልጦ ይታይ ነበር።
11. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
12. “የእስራኤላውያንን ማጒረምረም ሰምቻለሁ፤ ይህን ንገራቸው፤ ‘ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት ሥጋ ትበላላችሁ፤ ሲነጋም እንጀራ ትበላላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”
13. በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር።
14. ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ አመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ።
15. እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።ሙሴም፦ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው።
16. እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጐሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዞአል።
17. እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ።