ዘፀአት 11:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በፈርዖንና በግብፅ ላይ አንድ ሌላ መቅሠፍት አወርድባቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ፈርዖን ይለቃችኋል፤ ሲለቃችሁም አንዳችሁን ሳያስቀር ያስወጣችኋል።

2. ለእስራኤል ሕዝብ ለወንዶቹም ሆነ ለሴቶቹ የብርና የወርቅ ዕቃዎች ከየጐረቤቶቻቸው ስጡን ብለው እንዲወስዱ ንገራቸው።

3. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እስራኤላውያን በግብፃውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ አደረጋቸው። ሙሴም በግብፅ ምድር በፈርዖን ሹማምትና በመላው ሕዝብ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ሆነ።

4. ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እኩለ ሌሊት ሲሆን በመላው የግብፅ ምድር ላይ አልፋለሁ።

5. በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን ልጅ አንሥቶ የወፍጮ መጅ ገፊ እስከ ሆነችው እስከ ባሪያይቱ ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር በኵር ሆኖ የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ ይሞታል፤ እንዲሁም የቀንድ ከብቱ በኵር በሙሉ ያልቃል።

ዘፀአት 11