ዘዳግም 28:51-63 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

51. እስክትጠፋም ድረስ የእንስሳትህን ግልገልና የምድርህን ሰብል ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅ ሆነ ዘይት፣ የመንጋህን ጥጃ ሆነ፣ የበግና ፍየል መንጋህን ግልገል አያስቀርልህም።

52. የምትታመንባቸውን ታላላቅ የተመሸጉ ቅጥሮች እስኪወድቁ ድረስ በመላው አገርህ ያሉትን ከተሞችህን ሁሉ ይከባል፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ያሉትን ከተሞች በሙሉ ይወራቸዋል።

53. ጠላቶችህ ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ ከሥቃይ የተነሣ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰጠህን፣ የወገብህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ።

54. ሌላው ይቅርና በመካከልህ በጣም ደግና ርኅሩኅ የሆነው ሰው እንኳ ለገዛ ወንድሙ ወይም ለሚወዳት ሚስቱ ወይም ለተረፉት ልጆቹ አይራራላቸውም።

55. ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ላይም ቅንጣት ታህል እንኳ ከእነርሱ ለአንዱ አያቀምስም፤ ከተሞችህ ሁሉ በመከበባቸው ጠላቶችህ ከሚያደርሱብህ ሥቃይ የተነሣ ለእርሱ የቀረለት ይህ ብቻ ነውና።

56. በመካከልህ ተለሳልሳና ተቀማጥላ የምትኖር፣ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ፣ እግሯን ዐፈር ነክቶት የማያውቅ ሴት፣ የምትወደውን ባሏን፣ የገዛ ወንድ ወይም ሴት ልጆቿን ትንቃለች።

57. ከማሕፀኗ የወጣውን እንግዴ ልጇንና የምትወልዳቸውን ሕፃናት ትጠየፋለች፤ ይህን የምታደርገውም በመከራው ወቅት ጠላቶችህ ከተሞችህን ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ እነርሱን ደብቃ ለመብላት ስትል ነው።

58. በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የዚህን ሕግ ቃሎች በጥንቃቄ ባትከተልና አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የአምላክህንየእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስም ባታከብር፣

59. እግዚአብሔር (ያህዌ) አስፈሪ መቅሠፍት፣ አስጨናቂና ለብዙ ጊዜ የሚቈይ መዓት፣ አሠቃቂና በቀላሉ የማይወገድ ደዌ በአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል።

60. የምትፈራቸውንም የግብፅ በሽታዎች ሁሉ ያመጣብሃል፤ በአንተም ላይ ይጣበቃሉ።

61. ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ የሕግ መጽሐፍ ያልተጻፈውን ማንኛውንም ዐይነት ደዌና መከራ እስክትጠፋ ድረስ ያመጣብሃል።

62. ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስላልታዘዛችሁ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችሁ የነበራችሁት እናንተ ጥቂት ብቻ ትቀራላችሁ።

63. እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በማበልጸግና ቊጥራችሁን በማብዛት ደስ እንደ ተሰኘ፣ እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስም ደስ ይለዋል፤ ልትወርሷት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።

ዘዳግም 28