ዘዳግም 27:12-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዮሴፍና ብንያም ሕዝቡን ለመባረክ በገሪዛን ተራራ ላይ ይቁሙ።

13. ሮቤል፣ ጋድ፣ አሴር፣ ዛብሎን፣ ዳንና ንፍታሌምም በጌባል ተራራ ላይ ለመርገም ይቁሙ።

14. ሌዋውያን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገሩ፦

15. “የእጅ ጥበብ ባለ ሙያ የሠራውን፣ በእግዘአብሔር (ያህዌ) ዘንድ አስጸያፊ የሆነውን ምስል የሚቀርጽ ወይም ጣዖትን የሚያበጅ፣ በስውርም የሚያቆም ሰው የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

16. “አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን! ይበል።

17. “የባልንጀራውን የድንበር ድንጋይ ከቦታው የሚያንቀሳቅስ የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

18. “ዐይነ ስውሩን በተሳሳተ መንገድ የሚመራ፣ የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

19. “በመጻተኛው፣ አባት በሌለውና በመበለቲቱ ላይ ፍትሕ የሚያዛባ የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

20. “ከአባቱ ሚስት ጋር የሚተኛ የተረገመ ይሁን፤ የአባቱን መኝታ ያረክሳልና።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

21. “ከማናቸውም እንስሳ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚያደርግ የተረገመ ይሁን።ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

22. “የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ ከሆነችው እኅቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽም የተረገመ ይሁን።”ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።

ዘዳግም 27