1. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በአቢብ ወር ከግብፅ በሌሊት ስላወጣህ፣ የአቢብን ወር ጠብቅ፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፋሲካ አክብርበት።
2. እግዚአብሔር (ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ ከበግና ከፍየል ወይም ከመንጋህ አንዱን እንስሳ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፋሲካ አድርገህ ሠዋው።
3. ከቦካ ቂጣ ጋር አትብላው፤ ከግብፅ የወጣኸው በችኮላ ነውና ከግብፅ የወጣህበትን ጊዜ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ታስብ ዘንድ የመከራ ቂጣ ሰባት ቀን ብላ።
4. በምድርህ ሁሉ ላይ በአንተ ዘንድ ለሰባት ቀን እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ዕለት ምሽት ከምትሠዋውም ላይ ማናቸውንም ሥጋ ጧት ድረስ እንዲቈይ አታድርግ።
5. አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ በማናቸውም ከተማ ፋሲካን መሠዋት አይገባህም፤
6. ነገር ግን ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ፣ ፀሓይ ስትጠልቅ ምሽቱ ላይ ከግብፅ በወጣህበት ሰዓት ዓመታዊ መታሰቢያ በዚያ ፋሲካን ሠዋ።
7. ሥጋውንም ጠብሰህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብላ፤ ሲነጋም ወደ ድንኳንህ ተመልሰህ ሂድ።
8. ስድስት ቀን ያልቦካ ቂጣ ብላ፤ በሰባተኛው ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የተቀደሰ ጉባኤ አድርግ፤ ሥራም አትሥራበት።
9. እህልህን ማጨድ ከምትጀምርበት ዕለት አንሥቶ ሰባት ሳምንት ቊጠር፤
10. ከዚያም በኋላ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በባረከህ መጠን፣ በፈቃድህ የምታመጣውን ስጦታ በማቅረብ በመከሩ በዓል አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አክብር።
11. አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ በመካከልህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበላችሁ።
12. አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህንንም በጥንቃቄ ጠብቅ።
13. የእህልህን ምርት ከዐውድማህ፣ ወይንህንም ከመጭመቂያህ ከሰበሰብህ በኋላ፣ የዳስን በዓል ሰባት ቀን አክብር።
14. በበዓልህ አንተ፣ ወንድና ሴት ልጅህ፣ ወንድና ሴት አገልጋይህ፣ በከተማው ያለ ሌዋዊ፣ መጻተኛ፣ አባት አልባውና መበለቲቱ ደስ ይበላችሁ።