1. በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀርጸህ ወደ እኔ ወደ ተራራው ላይ ውጣ፤ ታቦትም ከዕንጨት ሥራ።
2. እኔም አንተ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት በእነዚህኞቹ ጽላቶች ላይ እጽፋቸዋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታኖራቸዋለህ።”
3. ስለዚህ ከግራር ዕንጨት ታቦት ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቀረጽሁ፤ ሁለቱንም ጽላቶች በእጆቼ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ።
4. እግዚአብሔር (ያህዌ) በስብሰባው ቀን፣ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የተናገራቸውንና ቀድሞ ጽፎአቸው የነበሩትን ዐሥሩን ትእዛዛት በእነዚህ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ።
5. ከዚያም ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘኝ መሠረት በሠራሁት ታቦትም ውስጥ፣ ጽላቶቹን አስቀመጥኋቸው፤ አሁንም እዚያ ናቸው።