1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2. “ከተቀጠቀጠ ብር ሁለት መለከት አብጅ፤ ማኅበረ ሰቡን ለመጥሪያና ከሰፈራቸው እንዲነሡም ለመቀስቀሻ አድርጋቸው።
3. ሁለቱ መለከቶች ሲነፉ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አንተ ዘንድ ይሰብሰብ፤
4. ነገር ግን አንዱ መለከት ብቻ ከተነፋ አለቆች ማለት የእስራኤል ጐሣ መሪዎች አንተ ዘንድ ይሰብሰቡ፤
5. መለከቱ ከፍ ባለ ድምፅ ሲነፋ በስተ ምሥራቅ የሰፈሩት ነገዶች ጒዞ ይጀምሩ፤
6. መለከቱ ከፍ ባለ ድምፅ ለሁለተኛ ጊዜ ሲነፋ በስተ ደቡብ የሰፈሩት ነገዶች ጒዞ ይጀምሩ፤ ከፍ ያለው ድምፅ ጒዞ ለመጀመር ምልክት ይሆናል።