6. ለአምላካቸው (ኤሎሂም) የተቀደሱ ይሁኑ፤ የአምላካቸውንም (ኤሎሂም) ስም አያርክሱ። ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርበውን መሥዋዕት የአምላካቸውን (ኤሎሂም) ምግብ ስለሚያቀርቡ ቅዱሳን ይሁኑ።
7. “ ‘ካህናት በዝሙት የረከሱትንም ሆነ ከባሎቻቸው የተፋቱትን ሴቶች አያግቡ፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሱ ናቸውና።
8. የአምላክህን (ኤሎሂም) ምግብ የሚያቀርብ ነውና ቀድሰው፤ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) ቅዱስ ነኝና ቅዱስ ይሁንላችሁ።
9. “ ‘የካህን ሴት ልጅ ዝሙት አዳሪ ሆና ራሷን ብታረክስ፣ አባቷን ታዋርዳለች፤ በእሳት ትቃጠል።
10. “ ‘ከወንድሞቹ መካከል ተለይቶ በራሱ ላይ ዘይት የፈሰሰበትና የክህነት ልብስ እንዲለብስ የተቀባው ካህን የራስ ጠጒሩን አይንጭ፤ ወይም ልብሱን አይቅደድ።
11. አስከሬን ወዳለበት ስፍራ አይግባ፤ ስለ አባቱም ሆነ ስለ እናቱ ራሱን አያርክስ።
12. የተቀደሰበት የአምላኩ (ኤሎሂም) የቅባት ዘይት በላዩ ስለ ሆነ የአምላኩን (ኤሎሂም) መቅደስ ትቶ በመሄድ መቅደሱን አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
13. “ ‘ካህኑ የሚያገባት ሴት ድንግል ትሁን።
14. ባል የሞተባትን፣ የተፋታችውን ወይም በዝሙት ዐዳሪነት የረከሰችውን ሴት አያግባ፤ ነገር ግን ከወገኖቹ መካከል ድንግሊቱን ያግባ።
15. በወገኖቹ መካከል ዘሩን አያርክስ። እርሱን የምቀድሰው እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ”