1. እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች ተዋደዱ።
2. እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ፣ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና።
3. በእስር ላይ ያሉትን ከእነርሱ ጋር እንደታሰራችሁ ሆናችሁ ዐስቡአቸው፤ እንዲሁም በሰው እጅ የሚንገላቱትን ራሳችሁ መከራ እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ ዐስቡአቸው።
4. ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች ሁሉ ላይ ይፈርዳል።
5. ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣“ከቶ አልተውህም፤በፍጹም አልጥልህም” ብሎአል።
6. ስለዚህ በሙሉ ልብ፣“ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።
7. የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው።