ኤርምያስ 51:26-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ከአንቺ ለማእዘን የሚሆን ድንጋይ፣ለመሠረትም የሚሆን ዐለት አይወሰድም፤ለዘላለም ባድማ ትሆኛለሽ፤”ይላል እግዚአብሔር።

27. “በምድር ሁሉ ላይ ሰንደቅ ዐላማ አንሡ!በሕዝቦች መካከል መለከትን ንፉ!ሕዝቦችን ለጦርነት በእርሷ ላይ አዘጋጁ፤የአራራትን፣ የሚኒንና የአስከናዝን መንግሥታት፣ጠርታችሁ በእርሷ ሰብስቡአቸው፤የጦር አዝማች ሹሙባት፤ፈረሶችንም እንደ አንበጣ መንጋ ስደዱባት።

28. የሜዶንን ነገሥታት፣ገዦቿንና ባለሥልጣኖቿን ሁሉ፣በግዛታቸው ሥር ያሉትን አገሮች ሁሉ፣እነዚህን ሕዝቦች ለጦርነት አዘጋጁባት።

29. ሰው በዚያ መኖር እስከማይችል ድረስ፣የባቢሎንን ምድር ባድማ ለማድረግ፣ እግዚአብሔር በባቢሎን ላይ ያቀደው ስለሚጸና፣ምድር ትናወጣለች፤ በሥቃይም ትወራጫለች።

30. የባቢሎን ጦረኞች መዋጋት ትተዋል፤በምሽጎቻቸው ውስጥ ተቀምጠዋል፤ኀይላቸው ተሟጦአል፤እንደ ሴት ሆነዋል፤በማደሪያዎቿም እሳት ተለኵሶአል፤የደጇም መወርወሪያ ተሰብሮአል።

31. ከተማዪቱ ሙሉ በሙሉ መያዟን፣ለባቢሎን ንጉሥ ለመንገር፣አንዱ ወሬኛ ሌላውን ወሬኛ፣አንዱ መልእክተኛ ሌላውን መልእክተኛ ወዲያው ወዲያው ይከተላል፤

32. መልካዎቿ እንደተያዙ፣የወንዝ ዳር ምሽጎቿ እንደ ተቃጠሉ፣ወታደሮቿም እንደ ተደናገጡ ሊነግሩት ይሯሯጣሉ።”

33. የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የባቢሎን ሴት ልጅ በመረገጥ ላይ እንዳለ፣የእህል መውቂያ አውድማ ናት፤የመከር ወራቷም ፈጥኖ ይደርስባታል።

34. “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በላን፣አድቅቆ ፈጨን፤እንደ ባዶ ማድጋ አደረገን፤እንደ ዘንዶ ዋጠን፣እንደ ጣፋጭ በልቶን ሆዱን ሞላ፤በኋላም አንቅሮ ተፋን፤

35. የጽዮን ነዋሪዎች፣ እንዲህ ይላሉ፤“በሥጋችን ላይ የተፈጸመው ግፍ በባቢሎን ላይ ይሁን፤”ኢየሩሳሌም እንዲህ ትላለች፤“ደማችን በባቢሎን ምድር በሚኖሩት ላይ ይሁን።”

ኤርምያስ 51