ኤርምያስ 23:29-40 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. “ቃሌ እንደ እሳት፣ ድንጋይንም እንደሚያደቅ መዶሻ አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር።

30. “ስለዚህ ቃሌን እርስ በእርስ በመሰራረቅ ከእኔ እንደ ተቀበሉ አድርገው የሚናገሩትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

31. “አፈጮሌነታቸውን በመጠቀም፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ የሚሉትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤

32. “እነሆ፤ ሐሰተኛ ሕልም ተመርኵዘው ትንቢት የሚናገሩትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ ሳልልካቸው ወይም ሳልሾማቸው ደፍረው ውሸት ይናገራሉ፤ ሕዝቤንም ያስታሉ፤ ለዚህም ሕዝብ አንዳች አይረቡትም” ይላል እግዚአብሔር።

33. “ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም ምንድን ነው?’ ብለው ቢጠይቁ፣ ‘ሸክሙ እናንተ ናችሁ፤ እወረውራችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር’ ብለህ መልስላቸው።

34. ነቢይ ወይም ካህን ወይም ማንኛውም ሰው፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ እያለ ቢናገር፣ ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ።

35. እያንዳንዱ ለባልንጀራው ወይም ለዘመዱ፣ ‘እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠ?’ ወይም፣ ‘እግዚአብሔር ምን ተናገረ?’ ማለት ይገባዋል።

36. ከእንግዲህ ግን፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብላችሁ መናገር አይገባችሁም፤ ምክንያቱም ለሰው ሁሉ የገዛ ራሱ ቃል ሸክሙ ስለሚሆን፣ የአምላካችንን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን፣ የሕያው አምላክን ቃል ታጣምማላችሁ።

37. ስለዚህ ለነቢዩ፣ ‘እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠህ’ ወይም፣ ‘እግዚአብሔር ምን ተናገረህ?’ ትለዋለህ፤

38. ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብትሉ እንኳ፣ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ፣ “የእግዚአብሔር ሸክም” አትበሉ ብዬ ብነግራችሁም፣ እናንተ፣ “የእግዚአብሔር ሸክም” ብላችኋል፤

39. ስለዚህ እናንተን፣ እንዲሁም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ የሰጠኋትን ከተማ ጭምር ፈጽሜ እተዋችኋለሁ፤ ከፊቴ እጥላችኋለሁ፤

40. ለዘላለም የማይረሳ ዕፍረት፣ የዘላለምም ውርደት አመጣባችኋለሁ።

ኤርምያስ 23