1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2. “ሂድና ጮኸህ ይህን ለኢየሩሳሌም ጆሮ አሰማ፤“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤‘በወጣትነትሽ ጊዜ የነበረሽን ታማኝነት፣በሙሽርነትሽም ወራት እንዴት እንደ ወደድሽኝ፣በምድረ በዳ ዘር በማይዘራበት ምድር፣እንዴት እንደተከተልሽኝ አስታውሳለሁ።
3. እስራኤል ለእግዚአብሔር ቅዱስ ነበረች፤የመከሩም በኵር ነበረች፤የዋጧት ሁሉ በደለኞች ሆኑ፤መዓትም ደረሰባቸው’ ”ይላል እግዚአብሔር።
4. የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ወገን ሁላችሁ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
5. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“አባቶቻችሁ ከእኔ የራቁት፣ከንቱ ነገርን የተከተሉት፣ራሳቸውም ከንቱ የሆኑት፣ምን ጥፋት አግኝተውብኝ ነው?
6. እነርሱም፣ ‘ከግብፅ ምድር ያወጣን፣በወና ምድረ በዳ፣በጐድጓዳና በበረሓ መሬት፣በደረቅና በጨለማ ቦታ፣ሰው በማያልፍበትና በማይኖርበት ስፍራ፣የመራን እግዚአብሔር ወዴት ነው?’ ብለው አልጠየቁም።
7. እኔ፣ ፍሬዋንና በረከቷን እንድትበሉ፣ለም ወደ ሆነ መሬት አመጣኋችሁ፤እናንተ ግን መጥታችሁ ምድሬን አረከሳችሁ፤ርስቴንም ጸያፍ አደረጋችሁ።