5. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በሰው የሚታመን፣በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው።
6. በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፤መልካም ነገር ሲመጣ አያይም፤ሰው በሌለበት በጨው ምድር፣በምድረ በዳ በደረቅ ስፍራ ይቀመጣል።
7. “ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
8. በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ቅጠሉም ዘወትር እንደለመለመ ነው፤በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”
9. የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ፈውስም የለውም፤ማንስ ሊረዳው ይችላል?
10. “እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣ልብን እመረምራለሁ፤የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።”
11. ሀብትን በግፍ የሚያከማች ሰው፣ያልፈለፈለችውን ጫጩት እንደምትታቀፍ ቆቅ ነው፤በዕድሜው አጋማሽ ትቶት ይሄዳል፤በመጨረሻም ሞኝነቱ ይረጋገጣል።
12. የመቅደሳችን ስፍራ፣ከጥንት ጀምሮ ከፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው።