ኢዮብ 5:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. “እነሆ፤ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ተግሣጽ አትናቅ።

18. እርሱ ያቈስላል፤ ይፈውሳል፤እርሱ ይሰብራል፤ በእጁም ይጠግናል፤

19. እርሱ ከስድስት መቅሠፍት ይታደግሃል፤በሰባተኛውም ጒዳት አያገኝህም።

20. በራብ ጊዜ ከሞት፣በጦርነትም ከሰይፍ ያድንሃል።

21. ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ጥፋት ሲመጣም አትፈራም።

22. በጥፋትና በራብ ላይ ትሥቃለህ፤የምድርንም አራዊት አትፈራም።

23. ከሜዳ ድንጋዮች ጋር ትዋዋላለህና፤የዱር አራዊትም ከአንተ ጋር ይስማማሉ።

24. ድንኳንህ በሚያስተማምን ሁኔታ እንዳለ ታውቃለህ፤በረትህን ትቃኛለህ፤ አንዳችም አይጐድልብህም።

25. ዘሮችህ አያሌ እንደሚሆኑ፣የምትወልዳቸውም እንደ ሣር እንደሚበዙ ታውቃለህ።

26. የእህል ነዶ ጐምርቶ በወቅቱ እንደሚሰበሰብ፣ዕድሜ ጠግበህ ወደ መቃብር ትሄዳለህ።

27. “እነሆ፤ ይህን ሁሉ መርምረናል፤ እውነት ሆኖ አግኝተነዋል፤ስለዚህ ልብ በል፤ ተቀበለውም።”

ኢዮብ 5