1. “ሁሉን የሚችል አምላክ ለምን የፍርድ ቀን አይወስንም?እርሱን የሚያውቁትስ ለምን ያን ቀን እንዲያው ይጠባበቃሉ?
2. ሰዎች ድንበር ይገፋሉ፤የሰረቁትን መንጋ ያሰማራሉ።
3. የድኻ ዐደጉን አህያ ቀምተው ይሄዳሉ፤የመበለቲቱንም በሬ በመያዣነት ይወስዳሉ።
4. ችግረኛውን ከመንገድ ያስወግዳሉ፤የምድሪቱም ድኾች ይሸሸጋሉ።
5. በምድረ በዳ እንዳሉ የሜዳ አህዮች፣ድኾች ምግብ ፍለጋ ይራወጣሉ፤ከበረሓው ምድር ለልጆቻቸው ምግብ ይሻሉ።
6. ከሜዳ መኖ ይሰበስባሉ፤ከክፉዎች የወይን ቦታም ይቃርማሉ።
7. ዕራቍታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፤በብርድም ጊዜ የሚለብሱት የላቸውም።
8. ከተራራ በሚወርድ ዝናብ በስብሰዋል፤መጠለያ አጥተው ቋጥኝ ዐቅፈዋል።
9. አባት የሌለው ልጅ ከዕቅፍ ተነጥቋል፤የድኻውም ልጅ በዕዳ ተይዞአል።