ኢዮብ 21:2-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. “ቃሌን በጥንቃቄ ስሙ፤የምታጽናኑኝም በዚህ ይሁን፤

3. ንግግሬን በትዕግሥት አድምጡ፤ከተናገርሁ በኋላ፣ መሣለቅ ትችላላችሁ።

4. “በውኑ ቅርታዬ በሰው ላይ ነውን?ትዕግሥት ማጣትስ አይገባኝምን?

5. ተመልከቱኝና ተገረሙ፤አፋችሁን በእጃችሁ ለጒሙ።

6. ስለዚህ ነገር ባሰብሁ ቍጥር እደነግጣለሁ፤ሰውነቴም በፍርሀት ይንቀጠቀጣል።

7. ኀጢአተኞች ለምን በሕይወት ይኖራሉ?ለምን ለእርጅና ይበቃሉ? ለምንስ እያየሉ ይሄዳሉ?

8. ዘራቸው በዐይናቸው ፊት፣ልጆቻቸውም በዙሪያቸው ጸንተው ሲኖሩ ያያሉ፤

9. ቤታቸው ያለ ሥጋት በሰላም ይኖራል፤የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።

10. ኮርማቸው ዘሩ በከንቱ አይወድቅም፤ያስረግዛል፤ ላማቸውም ሳትጨነግፍ ትወልዳለች።

11. ልጆቻቸውን እንደ በግ መንጋ ያሰማራሉ፤ሕፃናታቸውም ይቦርቃሉ።

12. በከበሮና በክራር ይዘፍናሉ፤በዋሽንትም ድምፅ ይፈነጫሉ።

13. ዕድሜያቸውን በተድላ ያሳልፋሉ፤በሰላምም ወደ መቃብር ይወርዳሉ።

14. እግዚአብሔርንም እንዲህ ይሉታል፤ ‘አትድረስብን!መንገድህንም ማወቅ አንፈልግም።

15. እናገለግለው ዘንድ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ ማን ነው?ወደ እርሱ ብንጸልይስ ምን እናገኛለን?’

16. ይሁንና ብልጽግናቸው በእጃቸው አይደለም፤ከኀጢአተኞች ምክር እርቃለሁ።

17. “የኀጢአተኞች መብራት የጠፋው ስንት ጊዜ ነው?የእግዚአብሔር ቍጣ መከራ የመጣባቸው፣መቅሠፍትም የደረሰባቸው ስንት ጊዜ ነው?

18. በነፋስ ፊት እንዳለ ገለባ፣በዐውሎ ነፋስም እንደ ተወሰደ ዕብቅ የሆኑት ስንት ጊዜ ነው?

ኢዮብ 21