ኢዮብ 12:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እግዚአብሔርን ጠርቼ የመለሰልኝ ሰው ብሆንም፣ለባልንጀሮቼ መሣቂያ ሆኛለሁ፤ጻድቅና ያለ ነቀፋ ሆኜ እያለሁ፣ መሣቂያ ሆኛለሁ።

5. የደላቸው በመከራ ያፌዛሉ፤እግሩ የተንሸራተተውንም ይገፈትራሉ።

6. የቀማኞች ድንኳን አይታወክም፤አምላካቸውን በእጃቸው ይዘው እየዞሩም፣እግዚአብሔርንም እያስቈጡ በሰላም ይኖራሉ።

7. “እስቲ እንስሶችን ጠይቁ፤ ያስተምሯችኋል፤የሰማይ ወፎችንም ጠይቁ፣ ይነግሯችኋል፤

8. ለምድር ተናገሩ፤ ታስተምራችኋለች፤የባሕርም ዓሣ ይነግራችኋል።

9. የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?

10. የፍጥረት ሁሉ ሕይወት፣የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናትና፤

11. ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ፣ጆሮ ቃላትን አይለይምን?

12. ጥበብ ያለው በአረጋውያን ዘንድ አይደለምን?ማስተዋልስ ረጅም ዕድሜ ባላቸው ዘንድ አይገኝምን?

13. “ጥበብና ኀይል የእግዚአብሔር ናቸው፤ምክርና ማስተዋልም በእርሱ ዘንድ ይገኛሉ።

14. እርሱ ያፈረሰውን መልሶ የሚገነባ የለም፣እርሱ ያሰረውን የሚፈታ አይገኝም።

15. እርሱ ውሃን ቢከለክል፣ ድርቅ ይሆናል፤ቢለቀውም ውሃው ምድሪቱን ያጥለቀልቃል።

ኢዮብ 12