1. “ሕይወቴን እጅግ ጠላሁ፤ስለዚህም ማጒረምረሜን ያለ ገደብ እለቃለሁ፤በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።
2. እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፤በምን ላይ እንዳልተስማማን ንገረኝ እንጂ አትፍረድብኝ።
3. የክፉዎችን ዕቅድ በደስታ እየተቀበልህ፣እኔን ግን ስታስጨንቀኝ፣የእጅህንም ሥራ ስታዋርድ ደስ ይልሃልን?
4. አንተ ዐይንህ የሥጋ ለባሽ ዐይን ነውን?ሟች የሆነ የሰው ልጅ እንደሚያይ ታያለህን?
5. ዘመንህ እንደ ሟች ሰው ዘመን ነውን?ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን?
6. ታዲያ፣ በደልን የምትፈላልግብኝ፣ኀጢአቴንም የምትከታተለው ለምንድን ነው?
7. እኔ በደለኛ እንዳልሆንሁ፣ከእጅህም ሊያስጥለኝ ማንም እንደማይችል አንተ ታውቃለህ።