26. ኢያሱ በጋይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋቸው ድረስ ጦር ያነጣጠረባትን እጁን አላጠፈም ነበር።
27. እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ኢያሱን ባዘዘው መሠረት፣ በከተማዪቱ ያገኙትን እንስሳትና ምርኮ ብቻ ለራሳቸው አደረጉ።
28. ስለዚህ ኢያሱ ጋይን አቃጠላት፣ እስከ ዛሬ እንደሚታየውም ለዘላለም የዐመድ ቊልልና ባድማ አደረጋት።
29. የጋይንም ንጉሥ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ሬሳውንም እስኪመሽ ድረስ እዚያው እንዳለ ተወው፤ ፀሓይ ስትጠልቅም፣ ኢያሱ ሬሳውን እንዲያወርዱትና በከተማው በር ላይ እንዲጥሉት አዘዘ፤ የትልልቅ ድንጋይ ቊልልም ከመሩበት፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛል።
30. ከዚያም ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ።