ኢያሱ 7:12-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. እንግዲህ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለመቋቋም ያልቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ጀርባቸውን አዙረው የሸሹትም ለጥፋት በመዳረጋቸው ነው። እርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ፣ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም።

13. “ተነሣ፤ ሕዝቡን ቀድስ፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እስራኤል ሆይ፤ እርም የሆነ ነገር በመካከላችሁ ስላለ፣ ይህን ካላስወገዳችሁ ጠላቶቻችሁን ለመቋቋም እንደማትችሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ለነገ ራሳችሁን ለማዘጋጀት ሰውነታችሁን ቀድሱ።

14. “ ‘ማለዳ በየነገድ በየነገዳችሁ ሆናችሁ ቅረቡ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ነገድ በየጐሣ በየጐሣው ሆኖ ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ይወጣል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር የሚለየው ጐሣ በየቤተ ሰቡ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል፤ እግዚአብሔር የሚለየው ቤተ ሰብ ደግሞ በግለሰብ በግለሰብ ሆኖ ወደ ፊት ይወጣል።

15. እርሙ የተገኘበት ሰው፣ እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሶአል፤ በእስራኤልም ዘንድ አሳፋሪ ተግባር ፈጽሞአልና።”

16. በማግሥቱ ጥዋት ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ እስራኤልንም በየነገድ በየነገዳቸው ሆነው እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም የይሁዳ ነገድ ተለየ፤

17. የይሁዳንም ጐሣዎች ወደ ፊት አቀረበ፤ ከእነዚህም የዛራን ጐሣ ለየ፤ እነዚህን ደግሞ በየቤተ ሰባቸው እንዲወጡ አደረገ፤ ከእነዚህም ዘንበሪ ተለየ።

18. ኢያሱ የዘንበሪን ቤተ ሰብ አባላት አንድ በአንድ ወደ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከዚያም ከይሁዳ ነገድ የሆነውም የዛራ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የከርሚ ልጅ አካን ለብቻው ተለየ።

19. ኢያሱም አካንን፣ “ልጄ ሆይ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ፤ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውን ሳትደብቅ ንገረኝ” አለው።

20. አካንም መልሶ ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እውነት ነው! የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ፤ ያደረግሁትም ይህ ነው፤

21. ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖር የመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅል ብርና ክብደቱ አምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም፤ ዕቃውም ብሩ ከታች ሆኖ፣ በድንኳኔ ውስጥ መሬት ተቀብሮአል።”

22. በዚህ ጊዜ ኢያሱ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ ሮጡ፤ በዚያም ብሩ ከታች ሆኖ ዕቃው እንደ ተቀበረ አገኙ።

23. ከድንኳኑም አውጥተው፣ ኢያሱና እስራኤላውያን ሁሉ ወዳሉበት አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩ።

24. ኢያሱም ከመላው እስራኤል ጋር ሆኖ፣ የዛራን ልጅ አካንን፣ ብሩን፣ ካባውን፣ የወርቁን ቡችላ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን፣ የከብቱን መንጋ፣ አህዮቹንና በጎቹን እንዲሁም ድንኳኑንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ወደ አኮር ሸለቆ አስወሰደ።

ኢያሱ 7