ኢያሱ 7:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እስራኤላውያን ግን እርም የሆነውን ነገር ለራሳቸው በመውሰድ በደሉ፤ ይህም ከይሁዳ ነገድ የሆነው አካን የከርሚ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የዛራ ልጅ እርም ከሆነው ነገር ስለ ወሰደ የእግዚአብሔር ቊጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ።

2. ኢያሱ ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ካለችው ከቤት አዌን አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ጋይ ከኢያሪኮ ሰዎችን ልኮ፣ “ወደዚያ ውጡ፤ አገሪቱንም ሰልሉ” አላቸው፤ ሰዎቹም ወጥተው ጋይን ሰለሉ።

3. ወደ ኢያሱም ተመልሰው፣ “ጋይን ለመውጋት ሕዝቡ ሁሉ መሄድ አያስፈልገውም፤ በዚያ ያለው ሕዝብ ጥቂት ስለ ሆነ፣ ከተማዪቱን ለመውጋት ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ሰው ስለሚበቃ ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ በመሄድ አይድከም” አሉት።

4. ስለዚህ ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጣ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሸ፤

5. የጋይም ሰዎች እስራኤላውያንንም ከከተማዪቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሽባሪም ድረስ በማባረር ቊልቊለቱ ላይ መቷቸው፤ ከእነርሱም ሠላሳ ስድስት ያህል ሰው ገደሉባቸው። ከዚህ የተነሣም የሕዝቡ ልብ ቀለጠ፤ እንደ ውሃም ፈሰሰ።

6. በዚህ ጊዜ ኢያሱ ልብሱን ቀደደ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፋ፤ የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንደዚሁ አደረጉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ።

7. ኢያሱም እንዲህ አለ፤ “ወዮ! ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ዮርዳኖስን አሻግረህ ይህን ሕዝብ ወደዚህ ያመጣኸው ለአሞራውያን አሳልፈህ በመስጠት እንዲያጠፉን ነውን? ምነው ሳንሻገር እዚያው ማዶ በቀረን ኖሮ!

8. ጌታ ሆይ፤ እስራኤል በጠላቱ ፊት ሲሸሽ እኔ ምን ልበል?

9. ከነዓናውያንና ሌሎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ ይህን ሲሰሙ ይከቡናል፤ ስማችንንም ከምድር ገጽ ያጠፉታል፤ እንግዲህ ስለ ታላቁ ስምህ ስትል የምታደርገው ምንድን ነው?”

10. እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ለምን በግንባርህ ተደፋህ?

11. እስራኤል በድሎአል፤ እንዲጠብቁ ያዘዝኋቸውን ቃል ኪዳኔን ጥሰዋል፤ እርም የሆነውን ነገር ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ዋሽተዋል፤ የወሰዱትንም ከራሳቸው ንብረት ጋር ደባልቀዋል።

ኢያሱ 7