1. በዚህ ጊዜ እስራኤላውያንን ከመፍራት የተነሣ፣ ኢያሪኮ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ ውጭ የሚወጣም ሆነ ወደ ውስጥ የሚገባ አልነበረም።
2. እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ኢያሪኮን ከንጉሥዋና ከተዋጊዎቿ ጋር አሳልፌ በእጅህ ሰጥቻለሁ።
3. ከተማዪቱን ከተዋጊዎቻችሁ ጋር አንድ ጊዜ ዙሩ፤ ይህንም ስድስት ቀን አድርጉ።
4. ሰባት ካህናት፣ ሰባት ቀንደ መለከት ተሸክመው በታቦቱ ፊት ይውጡ፤ በሰባተኛውም ቀን ካህናቱ መለከት እየነፉ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ይዙሩ።
5. የማያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ከፍ ያለ ጩኸት ያሰማ፤ ከዚያም የከተማዪቱ ቅጥር ይፈርሳል፤ ሕዝቡም ወደ ላይ ይወጣል፤ እያንዳንዱም ሰው በቀጥታ ይገባል።”
6. ስለዚህ የነዌ ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፣ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ሰባት ካህናትም ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው።
7. ሕዝቡንም፣ “ወደ ፊት ሂዱ፤ ከተማዋን ዙሩ፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ቀድመው ይሂዱ፤ ከተማዪቱንም ዙሩ” ሲል አዘዛቸው።