ኢያሱ 4:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እስራኤላውያንም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔር ለኢያሱ በነገረውም መሠረት፣ በእስራኤል ነገዶች ቊጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል አነሡ፤ ወደ ሰፈራቸውም ይዘው በመሻገር በዚያ አኖሯቸው።

9. ኢያሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ቆመውበት በነበረው በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ሌሎች ዐሥራ ሁለት ድንጋዮችን አቆመ፤ እነዚህም ድንጋዮች እስከ ዛሬ ድረስ በዚሁ ስፍራ ይገኛሉ።

10. ሙሴ ለኢያሱ በሰጠው መመሪያ መሠረት፣ እግዚእብሔር ለሕዝቡ እንUntitled eventዲነግር ኢያሱን ያዘዘው እስኪፈጸም ድረስ፣ ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት በዮርዳኖስ መካከል ቆመው ቈዩ፤ ሕዝቡም ፈጥነው ተሻገሩ፤

11. ሕዝቡ ሁሉ ተሻግረው እንዳበቁ፣ የእግዚአብሔር ታቦትና ካህናቱ፣ ሕዝቡ እያዩአቸው ተሻገሩ።

12. የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ፣ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ከእስራኤላውያን ፊት ቀድመው ተሻገሩ።

13. አርባ ሺህ ያህሉ ጦርና ጋሻቸውን ይዘው፣ ለውጊያ ዝግጁ ሆነው፣ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ኢያሪኮ ሜዳ ተሻገሩ።

14. በዚያች ዕለት እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደረገው፤ ሕዝቡ ሙሴን እንዳከበሩት ሁሉ፣ ኢያሱንም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አከበሩት።

15. ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤

16. “የምስክሩን ታቦት የተሸከሙትን ካህናት ከዮርዳኖስ ወንዝ እንዲወጡ እዘዛቸው።”

ኢያሱ 4