1. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ ካሳረፋቸው እነሆ፣ ብዙ ዘመን አለፈ፤ በዚህ ጊዜ ኢያሱ በጣም አርጅቶ፣ ዕድሜውም ገፍቶ ነበር፤
2. ኢያሱ እስራኤልን ሁሉ አለቆቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ፈራጆቻቸውንና ሹማምታቸውን በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ አርጅቻለሁ፤ ዕድሜዬም ገፍቶአል።
3. አምላካችሁ እግዚአብሔር ስለ እናንተ ሲል በእነዚህ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረገውን ማናቸውንም ነገር እናንተው ራሳችሁ አይታችኋል፤ ስለ እናንተ የተዋጋላችሁ ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነው።
4. ከዮርዳኖስ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ በሙሉ ካሸነፍኋቸው ሕዝቦች ያልወረሳችሁትን ቀሪ ምድር ርስት እንዲሆን ለየነገዶቻችሁ እንዴት አድርጌ በዕጣ እንዳከፋፈልኋችሁ አስታውሱ።
5. ራሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ከፊታችሁም ያሉበትን ስፍራ ያስለቅቃቸዋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁም ተስፋ መሠረት ምድራቸውን ትወርሳላችሁ።