ኢያሱ 18:11-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ለብንያም ነገድ የሆነው የመጀመሪያው ዕጣ በየጐሣ በየጐሣው ወጣ፤ በዕጣ የደረሳቸውም ምድር የሚገኘው በይሁዳና በዮሴፍ ነገዶች ርስት መካከል ሲሆን እንደሚከተለው ነው፤

12. በሰሜን ያለው ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ይነሣና የኢያሪኮን ሰሜናዊ ተረተር አልፎ፣ በስተ ምዕራብ ወዳለው ኰረብታማ ምድር በማምራት፣ እስከ ቤትአዌን ምድረ በዳ ይዘልቃል።

13. ከዚያ ደግሞ ወደ ደቡብ ሎዛ ማለት ወደ ቤቴል ተረተር ይሻገርና በታችኛው ቤትሖሮን በስተ ደቡብ ባለው ተራራ በኩል አድርጎ ወደ አጣሮት አዳር ይወርዳል።

14. በስተ ደቡብ ያለው ድንበር ከቤትሖሮን ትይዩ ካለው ኰረብታ ተነሥቶ፣ በምዕራብ በኩል ወደ ደቡብ በመታጠፍ፣ የይሁዳ ነገድ ከተማ ወደሆነችው ወደ ቂርያትበኣል ማለት ወደ ቂርያትይዓሪም ያልፋል፤ ይህ እንግዲህ በምዕራብ በኩል ያለው ድንበር ነው።

15. በስተ ደቡብ ያለው ድንበር ደግሞ በምዕራብ በኩል ከቂርያትይዓሪም ጥግ ይነሣና እስከ ነፍቶ ውሃ ምንጭ ይዘልቃል፤

16. ይኸው ድንበር ከራፋይም ሸለቆ በስተ ሰሜን ባለው በሄኖም ሸለቆ ትይዩ ቊልቊል ወደ ኰረብታው ግርጌ ይወርዳል፤ ከዚያም ከኢያቡሳውያን ከተማ በደቡብ በኩል ባለው ተረተር አድርጎ ወደ ሄኖም ሸለቆ በመውረድ እስከ ዓይንሮጌል ይዘልቃል።

17. ደግሞም ወደ ሰሜን ይታጠፍና በቤትሳሚስ በኩል አድርጎ እስከ ጌሊሎት ይዘልቃል፤ ከዚያም በአዱሚም መተላለፊያ ትይዩ እስካለው እስከ ሮቤል ልጅ እስከ ቦሀን ድንጋይ ይወርዳል።

18. ወደ ቤትዓረባ ሰሜናዊ ተረተር በመቀጠል ቊልቊል ወደ ዐረባ ይወርዳል።

19. ከዚያም ሰሜናዊን የቤትሖግላንን ተረተር አልፎ ይሄድና በስተ ደቡብ የዮርዳኖስ ወንዝ እስከሚገባበት እስከ ሙት የባሕር ወሽመጥ ይዘልቃል፤ ይህም ደቡባዊ ድንበሩ ነው።

20. በምሥራቅ በኩል ያለው ድንበር፣ ራሱ የዮርዳኖስ ወንዝ ነው።ይህ እንግዲህ የብንያም ነገድ ጐሣዎች በርስትነት የወረሷት ምድር ዳር ድንበሮቿ ሁሉ እነዚህ ነበሩ።

ኢያሱ 18