1. በዚያ ዘመን፣ በዚያ ጊዜ፣የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮ ስመልስ፣
2. አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ አወርዳቸዋለሁ፤ስለ ርስቴ፣ ስለ ሕዝቤ፣ ስለ እስራኤል፣በዚያ ልፈርድባቸው እገባለሁ፤ምድሬን ከፋፍለዋል፤ሕዝቤንም በሕዝቦች መካከል በታትነዋልና።
3. በሕዝቤ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ወንዶች ልጆችን በዝሙት አዳሪዎች ለወጡ፤ወይን ጠጅ ለመጠጣትም፣ሴቶች ልጆችን ሸጡ።
4. “ጢሮስና ሲዶና እንዲሁም እናንተ የፍልስጥኤም ግዛቶች ሁሉ ሆይ፤ እንግዲህ በእኔ ላይ ምን አላችሁ? ስላደረግሁት ነገር ብድር ልትመልሱልኝ ነውን? የምትመልሱልኝ ከሆነ፣ በፍጥነትና በችኰላ እናንተ ያደረጋችሁትን በራሳችሁ ላይ መልሼ አደርግባችኋለሁ።
5. ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋል፤ የተመረጠውንም ንብረቴን ተሸክማችሁ ወደ ቤተ መቅደሳችሁ አስገብታችኋልና።