ኢሳይያስ 7:10-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እንደ ገናም እግዚአብሔር አካዝን እንዲህ አለው፤

11. “ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከእግዚአብሔር ከአምላክህ ለምን።”

12. አካዝ ግን፣ “አልለምንም፣ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ።

13. ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ፤ የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን?

14. ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።

15. ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል።

16. ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል።

17. ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው።”

18. በዚያን ቀን እግዚአብሔር ራቅ ካሉት ከግብፅ ወንዞች ዝንቦችን፣ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል።

19. እነርሱም በሙሉ መጥተው፣ በየበረሓው ሸለቆ፣ በየዐለቱ ንቃቃት፣ በየእሾኹ ቍጥቋጦና በየውሃው ጒድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ።

ኢሳይያስ 7