21. መጐናጸፊያህን አለብሰዋለሁ፤ መታጠቂያህን አስታጥቀዋለሁ፤ ሥልጣንህንም አስረክበዋለሁ። እርሱም በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ፣ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል።
22. የዳዊትን ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አደርጋለሁ፤ እርሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋም፤ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍትም።
23. በአስተማማኝ ስፍራ እንደ ካስማ እተክለዋለሁ፤ ለአባቱም ቤት የክብር ዙፋን ይሆናል።
24. የቤተ ሰቡ ክብር፣ ልጅና የልጅ ልጅ፣ እንዲሁም ከማሰሮ ጀምሮ እስከ ጋን ድረስ ያለ የቤት ዕቃ ሁሉ በርሱ ላይ ይንጠለጠላል።
25. “በዚያ ቀን” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ “በአስተማማኝ ስፍራ የተተከለ ካስማ ይነቀላል፤ ተሰብሮም ይወድቃል፤ በእርሱም ላይ የተንጠለጠለው ሸክም ወድቆ ይከሰከሳል፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።