ሰቆቃወ 4:9-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. በራብ ከሚሞቱት ይልቅ፣በሰይፍ የተገደሉት ይሻላሉ፤ምግብ በሜዳ ላይ ካለማግኘታቸው የተነሣ፣በራብ ደርቀው ያልቃሉ።

10. ሕዝቤ ባለቀበት ጊዜ፣ምግብ እንዲሆኑአቸው፣ርኅሩኆቹ ሴቶች በገዛ እጆቻቸው፣ልጆቻቸውን ቀቀሉ።

11. እግዚአብሔር ለመቅሠፍቱ መውጫ በር ከፈተ፤ጽኑ ቍጣውን አፈሰሰ፤መሠረትዋን እንዲበላ፣በጽዮን እሳት ለኰሰ።

12. ጠላቶችም ሆኑ ወራሪዎች፣የኢየሩሳሌምን በሮች ጥሰው ይገባሉ ብለው፣የምድር ነገሥታት፣ወይም ከዓለም ሕዝብ አንዳቸውም አላመኑም።

13. ይህ ግን ከነቢያት ኀጢአት፣ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኖአል፤በውስጧ፣የጻድቃንን ደም አፍስሰዋልና።

14. እንደ ታወሩ ሰዎች፣በየመንገዱ ላይ ይደናበራሉ፤ማንም ሰው ደፍሮ ልብሳቸውን መንካት እስከማይችል ድረስ፣በደም እጅግ ረክሰዋል።

15. ሰዎች “ሂዱ! እናንት ርኵሳን!” ብለው ይጮኹባቸዋል፤“ወግዱ! ወግዱ! አትንኩ!” ይሏቸዋል፤ሸሽተው በሚቅበዘበዙበትም ጊዜ፣በአሕዛብ መካከል ያሉ ሰዎች፣“ከእንግዲህ በዚህ መቀመጥ አይገባቸውም!” ይላሉ።

16. እግዚአብሔር ራሱ በትኖአቸዋል፤ከእንግዲህ ወዲያ አይጠብቃቸውም፤ካህናቱ አልተከበሩም፤ሽማግሌዎቹም ከበሬታ አላገኙም።

17. ከሁሉም በላይ በከንቱ ርዳታን ስንጠባበቅ፣ዐይኖቻችን ደከሙ፤ከግንብ ማማችን ላይ ሆነን፣ሊያድን ከማይችል ሕዝብ ርዳታ ጠበቅን።

18. ሰዎች እግር እግራችንን ተከታተሉን፤ስለዚህ በመንገዳችን መሄድ አልቻልንም፤መጨረሻችን ቀርቦአል፤ ቀኖቻችንም ተቈጥረዋል፤ፍጻሜያችን መጥቶአልና።

19. ከሰማይ ንስሮች ይልቅ፣ጠላቶቻችን ፈጣኖች ናቸው፤በተራሮች ላይ አሳደዱን፤በምድረ በዳም ሸመቁብን።

20. በእግዚአብሔር የተቀባው፣ የሕይወታችን እስትንፋስ፣በወጥመዳቸው ተያዘ፤በጥላው ሥር፣በአሕዛብ መካከል እንኖራለን ብለን አስበን ነበር።

ሰቆቃወ 4