ምሳሌ 16:13-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ነገሥታት በታማኝ ከንፈሮች ደስ ይላቸዋል፤እውነት የሚናገረውን ሰው ይወዱታል።

14. የንጉሥ ቊጣ የሞት መልእክተኛ ነው፤ጠቢብ ሰው ግን ቊጣውን ያበርዳል።

15. የንጉሥ ፊት ሲፈካ ሕይወት አለ፤በጎነቱም ዝናብ እንዳዘለ የበልግ ደመና ነው።

16. ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!

17. የቅኖች ጐዳና ከክፋት የራቀ ነው፤መንገዱንም የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል።

18. ትዕቢት ጥፋትን፣የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች።

19. በተዋረደ መንፈስ ከተጨቈኑት ጋር መሆን፣ከትዕቢተኞች ጋር ብዝበዛን ከመካፈል ይሻላል።

20. ምክርን የሚሰማ ይለመልማል፤ በእግዚአብሔርም የሚታመን ቡሩክ ነው።

21. ልባቸው ጠቢብ የሆነ አስተዋዮች ይባላሉ፤ደስ የሚያሰኙ ቃላትም ዕውቀትን ያዳብራሉ።

22. ማስተዋልን ገንዘብ ላደረጋት የሕይወት ምንጭ ናት፤ቂልነት ግን በተላሎች ላይ ቅጣት ታመጣባቸዋለች።

23. የጠቢብ ሰው ልብ አንደበቱን ይመራል፤ከንፈሮቹም ዕውቀትን ያዳብራሉ።

24. ደስ የሚያሰኝ ቃል የማር ወለላ ነው፤ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለዐጥንትም ፈውስ ነው።

25. ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል፤

ምሳሌ 16