ማቴዎስ 22:20-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው።

21. እነርሱም፣ “የቄሣር ነው” አሉት።እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።

22. ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።

23. የሙታን ትንሣኤ የለም ብለው የሚያምኑ ሰዱቃውያን በዚያኑ ቀን ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ ብለው ጠየቁት፤

24. “መምህር ሆይ፤ ሙሴ፣ ‘አንድ ሰው ከሚስቱ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት አግብቶ ለእርሱ ዘር ይተካለት’ ብሎአል።

25. በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ፣ ሚስቱን ወንድሙ አገባት፤

26. እንደዚሁ ደግሞ ሁለተኛውም፣ ሦስተኛውም እስከ ሰባተኛው ድረስ በዚህ ሁኔታ ሞቱ።

27. በመጨረሻ ሴትዮዋ ራሷ ሞተች።

28. ስለዚህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ቀን ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”

29. ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአሔርን ኀይል ስለማታውቁ ትስታላችሁ፤

30. ከትንሣኤ በኋላ ሰዎች እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም።

31. ስለ ሙታን ትንሣኤ ግን እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ የተናገራችሁን አላነበባችሁምን?

32. ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ።’ እግዚአብሔር የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።”

33. ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ በትምህርቱ ተደነቁ።

34. ኢየሱስ ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው ሰምተው፣ ፈሪሳውያን በአንድነት ተሰበሰቡ፤

35. ከእነርሱም አንድ የኦሪት ሕግ አዋቂ፣ ሊፈትነው ፈልጎ እንዲህ አለው፤

36. “መምህር ሆይ፤ ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትእዛዝ ነው?”

37. እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’

38. ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤

39. ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤

ማቴዎስ 22