1. ለእግዚአብሔር አዲስ ዝማሬ ዘምሩ፤ምድር ሁሉ፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
2. ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ስሙንም ባርኩ፤ማዳኑንም ነጋ ጠባ አውሩ።
3. ክብሩን በሕዝቦች መካከል፣ድንቅ ሥራውንም በሰዎች ሁሉ ፊት ተናገሩ።
4. እግዚአብሔር ታላቅ ነውና፤ ውዳሴም የሚገባው ነው፤ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ ይገባዋል።
5. የሕዝብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
6. ክብርና ግርማ በፊቱ ናቸው፤ብርታትና ውበትም በመቅደሱ ውስጥ አሉ።
7. የሕዝቦች ወገኖች ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ስጡ፤ክብርንና ብርታትን ለእግዚአብሔር ስጡ።
8. ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤ቍርባንን ይዛችሁ ወደ አደባባዩ ግቡ።
9. በተቀደሰ ውበት ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ምድር ሁሉ፤ በፊቱ ተንቀጥቀጡ።