1. እግዚአብሔር ይነሣ፤ ጠላቶቹ ይበተኑ፤የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ።
2. ጢስ እንደሚበንን፣እንዲሁ አብንናቸው።ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፣ክፉዎችም እንዲሁ ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ።
3. ጻድቃን ግን ደስ ይበላቸው፤በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት ያድርጉ፤ደስታንና ፍስሓን የተሞሉ ይሁኑ።
4. ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ለስሙም ተቀኙ፤በደመናት ላይ የሚሄደውን ከፍ አድርጉት፤ስሙ እግዚአብሔር በተባለው ፊት፣እጅግ ደስ ይበላችሁ።
5. እግዚአብሔር በተቀደሰ ማደሪያው፣ለድኻ አደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች ነው።