1. ኀያላን ሆይ፤ በውኑ ጽድቅ ከአፋችሁ ይወጣል?የሰው ልጆች ሆይ፤ በቅን ትፈርዳላችሁን?
2. የለም፤ በልባችሁ ክፋትን ታውጠነጥናላችሁ፤በእጃችሁም ዐመፅን በምድር ላይ ትጐነጒናላችሁ።
3. ክፉዎች በማሕፀን ሳሉ ከመንገድ የወጡ ናቸው፤ሲወለዱ ጀምሮ የተሳሳቱና ውሸታሞች ናቸው።
4. መርዛቸው እንደ እባብ መርዝ ነው፤አልሰማ ብላ ጆሮዋን እንደ ደፈነች እፉኝት ናቸው፤
5. ጆሮዋንም የደፈነችው የመተተኛውንወይም የጠቢቡን ደጋሚ ቃል ላለመስማት ነው።
6. አምላክ ሆይ፤ ጥርሳቸውን በአፋቸው ውስጥ ስበር፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንበሶቹን መንጋጋ አወላልቅ!
7. ፈጥኖ እንደሚያልፍ ወራጅ ውሃ ይጥፉ፤ቀስታቸውን ሲስቡ ፍላጻቸው ዱልዱም ይሁን።