መዝሙር 18:11-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ጨለማን መሰወሪያው፣ በዙሪያውም አጐበሩ አደረገው፤በዝናብ አዘል ጥቍር ደመናም ተሸፈነ።

12. በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ፣ደመናት፣ የበረዶ ድንጋይና መብረቅ ወጡ።

13. እግዚአብሔር ከሰማያት አንጐደጐደ፤ልዑልም ድምፁን አስተጋባ።

14. ፍላጻውን አስፈንጥሮ በተናቸው፤መብረቅ አዥጐድጒዶ አሳደዳቸው።

15. እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተግሣጽህ የተነሣ፣ከአፍንጫህም እስትንፋስ የተነሣ፣የባሕር ወለል ተገለጠ፤የዓለምም መሠረት ራቍቱን ቀረ።

16. ከላይ እጁን ወደ ታች ዘርግቶ ያዘኝ፤ከብዙ ጥልቅ ውሃም አወጣኝ፤

17. ከኀያላን ጠላቶቼ አዳነኝ፤ከእኔ ከሚበረቱ ባላንጣዎቼም ታደገኝ።

18. እነርሱ በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ።

19. ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ።

20. እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መልሶልኛል፤እንደ እጄ ንጽሕናም ከፍሎኛል፤

21. የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም።

22. ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ሥርዐቱን ከፊቴ አላራቅሁም።

23. በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ።

24. እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መጠን፣በፊቱም እንደ እጄም ንጽሕና ከፍሎኛል።

25. ከታማኙ ጋር ታማኝ ትሆናለህ፤እንከን ከሌለበት ጋር ያለ እንከን ትሆናለህ፤

26. ከንጹሑ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ለጠማማው አንተ ትጠምበታለህ።

27. አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤ትዕቢተኛውን ዐይን ግን ታዋርዳለህ።

28. እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴን ታበራለህ፤አምላኬ ሆይ፤ ጨለማዬን ብርሃን ታደርገዋለህ።

መዝሙር 18