መክብብ 2:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አሁንም አእምሮዬ በጥበብ እየመራኝ ራሴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት፣ ሞኝነትንም ለመያዝ ሞከርሁ፤ ሰዎች በአጭር የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ባለው ላይ ቢሠሩት ሊጠቅማቸው የሚችል ምን እንደሆነ ለማየት ፈለግሁ።

4. ታላላቅ ነገሮችን አከናወንሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይንንም ተከልሁ፤

5. አትክልትን ተከልሁ፤ የመዝናኛ ስፍራዎችን አዘጋጀሁ፤ በእነዚህም ላይ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶችን ሁሉ ተከልሁባቸው፤

6. የሚለመልሙ ዛፎችን ለቦይ የሚሆኑ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ሠራሁ።

7. ወንድና ሴት ባሪያዎችን ገዛሁ፤ በቤቴም የተወለዱ ሌሎች ባሪያዎች ነበሩኝ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ይልቅ ብዙ የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች ነበሩኝ።

8. ለራሴም ብርንና ወርቅን፣ የነገሥታትና የአውራጃዎችን ሀብት አካበትሁ፤ ወንድና ሴት አዝማሪዎች፣ የሰው መደሰቻ የሆኑ ቅምጦች ነበሩኝ።

9. ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሆንሁ፤ በዚህ ሁሉ ጥበቤ ከእኔ ጋር ነበረች።

10. ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም፤ለልቤም ምድራዊ ደስታን አልነፈግሁትም፤ልቤ በሠራሁት ሁሉ ደስ አለው፤ይህም የድካሜ ሁሉ ዋጋ ነበረ።

11. ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፤ከፀሓይ በታች ምንም ትርፍ አልነበረም።

12. ከዚያም ጥበብን፣እብደትንና ሞኝነትን ለመመርመር ሐሳቤን መለስሁ፤አስቀድሞ ከተደረገው በቀር፣ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል?

13. ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ ሁሉ፣ጥበብም ከሞኝነት እንደሚበልጥ ተመለከትሁ።

14. የጠቢብ ሰው ዐይኖች ያሉት በራሱ ውስጥ ነው፤ሞኝ ግን በጨለማ ውስጥ ይራመዳል፤ሆኖም የሁለቱም ዕድል ፈንታ፣አንድ መሆኑን ተገነዘብሁ።

መክብብ 2