መክብብ 2:18-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ከፀሓይ በታች የደከምሁበትን ነገር ሁሉ ጠላሁት፣ ከኋላዬ ለሚመጣው የግድ እተውለታለሁና።

19. እርሱ ጠቢብ ወይም ሞኝ ይሆን እንደሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም ከፀሓይ በታች ድካሜንና ችሎታዬን ባፈሰ ስሁበት ሥራ ሁሉ ላይ ባለቤት ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

20. ስለዚህ ከፀሓይ በታች በደከምሁበት ነገር ሁሉ ላይ ልቤ ተስፋ መቊረጥ ጀመረ፤

21. ምክንያቱም ሰው ሥራውን በጥበብ፣ በዕውቀትና በብልኀት ሠርቶ፣ ከዚያ ያለውን ሁሉ ለሌላ ላልለፋበት ሰው ይተውለታል። ይህም ደግሞ ከንቱና ትልቅ ጒዳት ነው።

22. ሰው ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ጥረትና ልፋት ሁሉ ትርፉ ምንድን ነው?

23. በዘመኑ ሁሉ ሥራው ሥቃይና ሐዘን ነው፤ በሌሊትም እንኳ ቢሆን አእምሮው አያርፍም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

24. ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደሚሰጥ አየሁ፤

25. ከእርሱ ዘንድ ካልሆነ ማን መብላትና መደሰት ይችላል?

26. እግዚአብሔር፣ ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብን፣ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል። ለኀጢአተኛ ግን፣ እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ይተውለት ዘንድ፣ ሀብትን የመሰብሰብና የማከናወን ተግባር ይሰጠዋል። ይህም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

መክብብ 2