መሳፍንት 9:7-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ የሴኬም ነዋሪዎች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ፤

8. ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፣ ‘አንተ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

9. የወይራ ዛፍም፣ “ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እግዚአብሔርና ሰዎች የሚከበሩበትን ዘይቴን መስጠት ልተውን?” አለ።

10. “ቀጥሎም ዛፎቹ በለስን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

11. “በለስ ግን፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እጅግ ጣፋጭና መልካም የሆነውን ፍሬዬን መስጠት ልተውን?’ አለ።

12. “ከዚያም ዛፎቹ የወይን ተክልን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

13. “የወይን ተክሉም፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ አማልክትንና ሰዎችን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጄን መስጠት ልተውን? አለ።

14. በመጨረሻም ዛፎቹ በሙሉ የእሾኽ ቊጥቋጦን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።

15. “የእሾኽ ቊጥቋጦውም ዛፎቹን፣ ‘በእርግጥ ቀብታችሁ በላያችሁ የምታነግሡኝ ከሆነ መጥታችሁ በጥላዬ ሥር ተጠለሉ፤ ይህን ባታደርጉ ግን እሳት ከእሾኽ ቊጥቋጦው ይነሣ! የሊባኖስንም ዝግባዎች ይብላ’ አላቸው።

16. “እንግዲህ አቤሜሌክን ስታነግሡት በቅንነትና በእውነት አድርጋችሁት ከሆነ፣ ይሩበኣልንና ቤተ ሰቡን በበጎ ዐይን ተመልክታችሁ ላደረገው የሚገባውን አይታችሁለት ከሆነ፣

17. አባቴ ለእናንተ መዋጋቱን፣ ከምድያማውያን እጅ ሊያድናችሁ ሕይወቱን መስጠቱን አሰባችሁ ማለት ነው።

18. ነገር ግን እናንተ ዛሬ በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ዐመፃችሁ፤ ሰባ ልጆቹን በአንዲት ድንጋይ ላይ ዐረዳችሁ፤ ዘመዳችሁ ስለ ሆነም አባቴ ከባሪያው የወለደውን ልጅ አቤሜሌክን በሴኬም ነዋሪዎች ላይ አነገሣችሁት።

19. እንግዲህ ዛሬ በይሩበኣልና በቤተ ሰቡ ላይ ያደረጋችሁት በእውነትና በቅንነት ከሆነ እናንተ በአቤሜሌክ ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም በእናንተ ደስ ይበለው!

20. ይህ ካልሆነ ግን እሳት ከአቤሜሌክ ትውጣና እናንተን፣ የሴኬምንና የቤት ሚሎን ነዋሪዎች ትብላ፤ እንዲሁም እሳት ከእናንተ፣ ከሴኬምና ከቤትሚሎን ነዋሪዎች ትውጣና አቤሜሌክን ትብላ።”

21. ከዚህ በኋላ ኢዮአታም ሸሽቶ አመለጠ፤ ብኤር ወደተባለች ቦታም መጣ፤ ወንድሙንም አቤሜሌክን ፈርቶ ስለ ነበር እዚያው ይኖር ጀመር።

22. አቤሜሌክ እስራኤልን ሦስት ዓመት ከገዛ በኋላ፣

23. እግዚአብሔር በአቤሜሌክና በሴኬም ነዋሪዎች መካከል ክፉ መንፈስ ሰደደ፤ ስለዚህም የሴኬም ሰዎች አቤሜሌክን ከዱት።

24. እግዚአብሔር ይህን ያደረገውም፣ በሰባው የይሩበኣል ልጆች ላይ ስለ ተፈጸመው ግፍና ስለ ፈሰሰው ደማቸው፣ ወንድማቸውን አቤሜሌክና ወንድሞቹን እንዲገድል የረዱትን የሴኬም ሰዎች ለመበቀል ነው።

25. የሴኬም ነዋሪዎችም አቤሜሌክን ሸምቀው የሚጠባ በቁትን ሰዎች መደቡ፤ ሰዎቹም እርሱን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በዚያ የሚያልፈውን ሁሉ ዘረፉ፤ ወሬውም ለአቤሜሌክ ደረሰው።

መሳፍንት 9