37. ገዓልም፣ “ተመልከት እንጂ ሕዝብ እኮ ከተራራው ወገብ ላይ እየደረሰ ነው፤ አንዱ ክፍልም በቃላተኞች ዛፍ በኩል አድርጎ እየመጣ ነው” ብሎ እንደ ገና ተናገረ።
38. ከዚያም ዜቡል፣ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜልክ ማን ነው? ብለህ የደነፋኸው አሁን የት አለ? ያቃለልሀቸውስ ሰዎች እነዚህ አይደሉምን? በል ውጣና ግጠማቸው” አለው።
39. ገዓል የሴኬምን ሰዎች መርቶ በመውጣት አቤሜሌክን ተዋጋው፤
40. ሆኖም አቤሜሌክ አሳደደው፤ እስከ መግቢያው በር ድረስ ባለው መንገድ ሲሸሹም ብዙ ሰዎች ቈስለው ወደቁ።
41. አቤሜሌክ በአሩማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን ከሴኬም አስወጣቸው።
42. በማግስቱ የሴኬም ሕዝብ ወደ ዕርሻ ወጡ፤ ይህም ለአቤሜሌክ ተነገረው፤
43. እርሱም ሰዎቹን አስከትሎ ወጣ፤ ከዚያም ሰዎቹን ሦስት ቦታ መድቦ በዕርሻዎቹ ውስጥ አድፍጠው እንዲጠባበቁ አደረገ። አቤሜሌክ የሴኬም ሰዎች ከከተማዪቱ መውጣታቸውን እንዳየም ካደፈጠበት ሊወጋቸው ተነሣ።
44. ከዚያም አቤሜሌክና አብረውት የነበሩ ምድቦች ቦታ ለመያዝ በፍጥነት ወደ ከተማዪቱ መግቢያ በሚሮጡበት ጊዜ፣ ሌሎቹ ሁለት ምድቦች ደግሞ እየሮጡ ሄደው በዕርሻው ያሉትን ሁሉ ፈጇቸው።
45. በዚያን ዕለት አቤሜሌክ ቀኑን ሙሉ ከተማዪቱን ሲወጋ ውሎ በመጨረሻ ያዛት፤ሕዝቧን ፈጀ፤ ከተማዪቱንም አጠፋ፤ በላይዋም ጨው ዘራባት።