1. የይሩባኣል ልጅ አቤሜሌክ ወደ እናቱ ወንድሞች ወደ ሴኬም ሄደ። እነርሱንና የእናቱን ጐሣዎች በሙሉ እንዲህ አላቸው፤
2. “የሴኬምን ነዋሪዎች ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ጠይቋቸው፤ ‘ሰባዎቹ የይሩባኣል ልጆች ቢገዟችሁ ይሻላል ወይስ አንድ ሰው ብቻ?’ የሥጋችሁ ቍራጭ፣ ያጥንታችሁ ፍላጭ መሆኔን ልብ በሉ።”
3. የእናቱ ዘመዶች ስለ እርሱ ሆነው እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለሴኬም ነዋሪዎች በሙሉ ነገሩ፤ አቤሜሌክንም ለመከተል ልባቸው ዳዳ፤ “እርሱማ ወንድማችን አይደል ብለዋልና”።
4. እነርሱም በኣልብሪት ቤተ ጣዖት ሰባ ሰቅል ናስ ሰጡት፤ አቤሜሌክም በዚያ ወሮበሎችንና ምናምንቴዎችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከተሉት።
5. ከዚያም ዖፍራ ወደሚገኘው ወደ አባቱ ቤት ሄደ፤ ሰባውን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ዐረዳቸው፤ የይሩበኣል የመጨራሻ ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ስለ ነበር አመለጠ።
6. የሴኬምና የቤት ሚሎ ነዋሪዎች በሙሉ አቤሜሌክን ለማንገሥ ሴኬም ውስጥ በዐምዱ አጠገብ ካለው የባሉጥ ዛፍ ሥር ተሰበሰቡ።
7. ኢዮአታም ይህ በተነገረው ጊዜ፣ በገሪዛን ተራራ ጫፍ ላይ ወጥቶ ድምፁን ከፍ በማድረግ እንዲህ አላቸው፤ የሴኬም ነዋሪዎች ሆይ፤ እግዚአብሔር ይሰማችሁ ዘንድ እኔን ስሙኝ፤
8. ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች የሚያነግሡትን ለመቀባት ወጡ፤ ወይራንም፣ ‘አንተ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
9. የወይራ ዛፍም፣ “ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እግዚአብሔርና ሰዎች የሚከበሩበትን ዘይቴን መስጠት ልተውን?” አለ።
10. “ቀጥሎም ዛፎቹ በለስን፣ ‘መጥተህ ንጉሣችን ሁን’ አሉት።
11. “በለስ ግን፣ ‘ከዛፎች በላይ ለመወዛወዝ ስል፣ እጅግ ጣፋጭና መልካም የሆነውን ፍሬዬን መስጠት ልተውን?’ አለ።