መሳፍንት 4:19-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ሲሣራም፣ “ጠምቶኛልና እባክሽን ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርሷም የወተት ጮጮውን ከፍታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤ እንደ ገናም ሸፈነችው።

20. እርሱም፣ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ፣ “እዚህ ሰው አለ?” ቢልሽ፣ “የለም በይ” አላት።

21. የሔቤር ሚስት ኢያዔል ግን ሲሣራ ደክሞ፣ ከባድ እንቅልፍም ወስዶት ሳለ፣ የድንኳን ካስማና መዶሻ ይዛ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ከዚያም ካስማውን በመዶሻ ጆሮ ግንዱ ላይ መትታ ከመሬት ጋር ሰፋችው፤ እርሱም ሞተ።

22. ባርቅ ሲሣራን በመከታተል ላይ ስለ ነበር ከዚያ ሲደርስ፣ ኢያዔል ከድንኳኗ ወጥታ “ና፤ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው፤ ስለዚህ ከእርሷ ጋር ወደ ድንኳንዋ ገባ፤ ሲሣራም በጆሮ ግንዱ ላይ ካስማ እንደ ተመታበት ሞቶ ተዘርሮ ነበረ።

23. በዚያች ዕለት እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤላውያን ፊት እንዲሸነፍ አደረገው፤

24. ከነዓናዊውን ንጉሥ ኢያቢስን እስኪደመስሱ ድረስ የእስራኤላውያን ክንድ እየበረታ ሄደ።

መሳፍንት 4