1. ከዚያም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉ እንዲሁም በገለዓድ ምድር የሚገኙ እስራኤላውያን ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው ወጡ፤ በምጽጳም በእግዚአብሔር ፊት ተሰበሰቡ።
2. የእስራኤል ሕዝብ ነገዶች ሁሉ ቍጥራቸው አራት መቶ ሺህ በሚሆን፣ ሰይፍ በሚመዙ እግረኞች ወታደሮች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ መካከል ተገኙ።
3. በዚህ ጊዜ ብንያማውያን፣ እስራኤላውያን ወደ ምጽጳ መውጣታቸውን ሰሙ፤ ከዚያም እስራኤላውያን፣ “ይህ ክፉ ድርጊት እንዴት እንደ ተፈጸመ እስቲ ንገሩን” ተባባሉ።
4. ስለዚህ የተገደለችው ሴት ባል ሌዋዊ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔና ቍባቴ በዚያ ለማደር በብንያም ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ መጣን።
5. የጊብዓም ሰዎች በሌሊት ሊገድሉኝ ያደርኩበትን ቤት ከበቡት፤ ከዚያም በቁባቴ ላይ ስለ አመነዘሩባት ሞተች።
6. የቁባቴንም ሬሳ ከቈራረጥሁ በኋላ እያንዳንዱን ቍራጭ፣ እያንዳንዱ የእስራኤል ርስት ወዳለበት አገር ሰደድሁ፤ ይህን ያደረግሁትም ሰዎቹ በእስራኤል ዘንድ አሠቃቂና አስነዋሪ ድርጊት ስለ ፈጸሙ ነው።