4. ከዚያም ወጥቶ በመሄድ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ የሁለት ሁለቱን ጭራ አንድ ላይ ካሰረ በኋላ ችቦ ወስዶ ጥንድ ሆኖ ከተያያዘው ጭራ ጋር አሰረው።
5. ችቦውን በእሳት አቀጣጥሎ ቀበሮቹን በፍልስጥኤማውያን የእህል አዝመራ ላይ ለቀቃቸው፤ ነዶውንና የቆመውን አዝመራ እንዲሁም የወይኑንና የወይራውን ተክል አቃጠለ።
6. ፍልስጥኤማውያን፣ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ፣ “ሚስቱ ለሚዜው ስለ ተሰጠችበት የተምናዊው ዐማች ሳምሶን ነው” የሚል መልስ አገኙ።ስለዚህም ፍልስጥኤማውያን ወጥተው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጥለው ገደሏቸው።
7. ሳምሶንም፣ “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ ሳልበቀላችሁ አልመለስም” አለ።
8. ክፉኛ መታቸው፤ ከነርሱም ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚያም ወርዶ በኢታም ዐለት ዋሻ ተቀመጠ።
9. ፍልስጥኤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ከዚያም በሌሒ አጠገብ ተበታትነው አደፈጡ።
10. የይሁዳም ሰዎች፣ “ልትወጉን የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው።እነርሱም “እኛ የመጣነው ሳምሶንንልና ስርና ያደረገብንን ልናደርግበት ነው” ብለው መለሱላቸው።
11. ከዚያም ሦስት ሺህ ሰዎች ከይሁዳ ተነሥተው በኤታም ዐለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሳምሶንን፣ “ፍልስጥኤማውያን ገዦቻችን መሆናቸውን አታውቅምን? ያደረግህብንስ ነገር ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።ሳምሶንም፣ “ያደረግሁት እነርሱ ያደረጉብኝን ነው” በማለት መለሰላቸው።
12. እነርሱም፣ “አስረን ለፍልስጥኤማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት።ሳምሶንም፣ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው።
13. እነርሱም፣ “አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ ራሳችን አንገድልህም” አሉት፤ ከዚያ በሁለት አዳዲስ ገመድ አስረው ከዐለቱ ዋሻ አወጡት።
14. ሳምሶን ሌሒ እንደ ደረሰም ፍልስጥኤማውያን እየጮኹ ወደ እርሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ።
15. ከዚያም በቅርቡ የሞተ የአንድ የአህያ መንጋጋ አይቶ ከመሬት አነሣ፤ በዚያም አንድ ሺህ ሰው ገደለ።
16. ሳምሶንም፣“በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ሺህ ሰው ዘራሪ፤በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ሺህ ሬሳ አነባባሪ፡ ብሎ ፎከረ።