መሳፍንት 11:19-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. “ከዚያም እስራኤል በሐሴቦን ወዳለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞች ልኮ፣ ‘ወደ ገዛ ስፍራችን ለመሄድ በአገርህ እንዳልፍ ፍቀድልኝ’ አለው።

20. ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ ሰራዊቱንም ሰብስቦ በያሃድ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ።

21. “ከዚያም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ አሸነፏቸውም፤ እስራኤልም በዚያ አገር የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሰ፤

22. ከአርኖን እስከ ያቦቅ፣ ከምድረ በዳው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን ምድር በሙሉ ወረሱ።

23. እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሳዶ ካስወጣቸው፣ አንተ ለመውሰድ ምን መብት አለህ?

24. አምላክህ ካሞሽ የሰጠህን ይዞ ማቈየቱ ያንተ ፈንታ ነው፤ እኛም እንደዚሁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰጠንን ሁሉ ርስት አድርገን እንወርሳለን።

25. አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? ለመሆኑ እርሱ ከእስራኤል ጋር ተጣልቶአልን? ወይስ ተዋግቶአልን?

26. እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮቿ፣ በአሮዔርና በመንደሮቿ፣ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረበት በዚያን ጊዜ ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር?

27. እኔ አልበደልሁህም፤ አንተ ግን በእኔ ላይ ዘምተህ በድለኸኛል፤ እንግዲህማ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤላውያንና በአሞናውያን መካከል ዛሬ ይፍረድ።”

28. የአሞን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከውን መልእክት ከምንም አልቈጠረውም።

29. ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ተነሥቶም ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ፤ ገለዓድ ባለችው በምጽጳ በኩል አድርጎም በአሞናውያን ላይ ዘመተባቸው።

30. ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፣

31. አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።”

32. ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ እግዚአብሔርም እርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው።

33. ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባቢ ከዚያም አልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ።

34. ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ፤ እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከእርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም።

35. ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፣ “ወይኔ ልጄ ጒድ አደረግሽኝ! ጭንቅም ላይ ጣልሺኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለእግዚአብሔር ተስያለሁና” ብሎ በኀዘን ጮኸ።

36. እርሷም እንዲህ አለች፤ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለእግዚአብሔር ቃል ገብተሃል፤ ጠላቶችህን አሞናውያንን አሁን እግዚአብሔር ተበቅሎልሃልና ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ።

37. ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤ ከእንግዲህ ባል ስለማላገባ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደ ተራሮች ወጥቼ እየዞርሁ ሁለት ወር እንዳለቅስ አሰናብተኝ።”

38. እርሱም፣ “በይ ሂጂ” ብሎ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርሷም ከእንግዲህ ባል ስለማታገባ ከልጃገረድ ጓደኞቿ ጋር ወደ ተራሮች ሄደው አለቀሱ።

መሳፍንት 11