ሕዝቅኤል 40:31-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

31. መተላለፊያ በረንዳው ከውጭው አደባባይ ጋር ትይዩ ነው፤ የዘምባባ ዛፎች በዐምዶቹ ላይ ተቀርጸዋል፤ እስከ መግቢያው ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

32. ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ መግቢያ በሩንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

33. የዘብ ቤቶቹ፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ መግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳው ዙሪያውን መስኮቶች ነበሩት፤ የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

34. መተላለፊያ በረንዳው ከውጩ አደባባይ ትይዩ ነው፤ በዐምዶቹ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል፤ እስከ መግቢያ ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

35. ከዚያም ወደ ሰሜን በር አመጣኝ፤ ለካውም፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

36. የዘብ ቤቶቹ፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦቹና መተላለፊያ በረንዳው መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩት። የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

37. መተላለፊያ በረንዳው ከውጩ አደባባይ ትይዩ ነው፤ በዐምዶቹም ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል፤ እስከ መግቢያው ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

38. በእያንዳንዱ የውስጥ መግቢያ በር መተላለፊያ በረንዳ አጠገብ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚታጠብበት በር ያለው ክፍል አለ።

39. በመግቢያው በር ላይ ባለው መተላለፊያ በረንዳው ሥር በግራና በቀኝ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የኀጢአትና የበደል መሥዋዕት የሚታረዱበት ሁለት ሁለት ጠረጴዛዎች አሉ።

ሕዝቅኤል 40