24. “ ‘ከአሕዛብ መካከል አስወጣችኋለሁ፤ ከየአገሩ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራችሁም መልሼ አመጣችኋለሁ።
25. ንጹሕ ውሃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ንጹሕ ትሆናላችሁ፤ ከርኵሰታችሁ ሁሉና ከጣዖታቶቻችሁ ሁሉ አነጻችኋለሁ።
26. አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።
27. መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥርዐቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ።
28. ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝቤም ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋሁ።
29. ከርኵሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራለሁ፤ አበዛዋለሁም፤ ራብንም አላመጣባችሁም።
30. ከራብ የተነሣ በአሕዛብ መካከል በውርደት እንዳትሳቀቁ፣ የዛፉን ፍሬና የዕርሻውን ሰብል አበዛለሁ።
31. ከዚያም ክፉ መንገዳችሁንና የረከሰ ሥራችሁን ታስታውሳላችሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁና ስለ አስጸያፊ ድርጊታችሁ ራሳችሁን ትጠላላችሁ።
32. ለእናንተ ስል ይህን እንደማላደርግ እንድታውቁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአድራጎታችሁ ዕፈሩ፤ ተሸማቀቁ!
33. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከኀጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ቀን፣ ከተሞቻችሁ እንደ ገና መኖሪያ ይሆናሉ። የፈረሱትም እንደ ገና ይታደሳሉ።
34. በዐላፊ አግዳሚው ዐይን ጠፍ ሆኖ ይታይ የነበረው፣ ባድማ መሬት ይታረሳል።
35. እነርሱም፣ “ጠፍ የነበረው ይህ ምድር እንደ ዔድን ገነት መሰለ፤ የተደመሰሱ፣ የፈራረሱና ባድማ የሆኑት ከተሞች አሁን መኖሪያና ምሽግ ሆነዋል” ይላሉ።