ሕዝቅኤል 1:15-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ሕያዋን ፍጡራኑን ስመለከታቸው፣ አራት ፊቶች ባሉት በእያንዳንዱ ፍጡር አጠገብ አንዳንድ መንኰራኵር በምድር ላይ አየሁ።

16. የመንኰራኵሮቹ መልክና አሠራር እንዲህ ነበር፤ እንደ ቢረሌ ያንጸባርቁ ነበር፤ የአራቱም ቅርጽ ተመሳሳይ ሆኖ፤ እያንዳንዱ መንኰራኵር በመንኰራኵር ውስጥ ተሰክቶ የተሠራ ይመስል ነበር።

17. በሚሄዱበት ጊዜም፣ ፍጡራኑ ወደሚዞሩበት ወደ አራቱ አቅጣጫ ሁሉ መንቀሳቀስ ይችሉ ነበር፤ ፍጡራኑ በሚሄዱበትም ጊዜ መንኰራኵሮቹ ወዲያና ወዲህ አይሉም ነበር።

18. የመንኰራኵሮቹ ክብ ጠርዝ ረጅምና አስፈሪ ነበር፤ የአራቱም መንኰራኵሮች ክብ ጠርዝ ዙሪያውን በዐይኖች የተሞላ ነበር።

19. ሕያዋኑ ፍጡራን ሲንቀሳቀሱ፣ በአጠገባቸው ያሉ መንኰራኵሮችም ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ሕያዋኑ ፍጡራን ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ፣ መንኰራኵሮቹም አብረዋቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።

20. መንፈስ ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዳሉ፤ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ መንኰራኵሮቹ አብረዋቸው ይነሣሉ፤

21. ፍጡራኑ ሲንቀሳቀሱ ይን ቀሳቀሳሉ፤ ፍጡራኑ ቀጥ ብለው ሲቆሙ እነርሱም ይቆማሉ፤ ፍጡራኑ ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ፣ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ መንኰራኵሮቹ አብረዋቸው ይነሣሉ።

22. ከሕያዋኑ ፍጡራን ራስ በላይ የሚያስፈራና፤ እንደ በረዶ የሚያንጸባርቅ ጠፈር የሚመስል ነገር ነበር።

23. ከጠፈሩም በታች የአንዱ ክንፍ ወደ ሌላው ተዘርግቶ ነበር፤ እያንዳንዱም ሰውነቱን የሚሸፍንበት ሁለት ክንፍ ነበረው።

24. ፍጡራኑ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የክንፎቻቸውን ድምፅ ሰማሁ፤ ድምፁም እንደሚጐርፍ ውሃ ጩኸት፣ ሁሉን እንደሚችል አምላክ ድምፅና እንደ ሰራዊት ውካታ ነበር። መንቀሳቀሳቸውን ሲያቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

25. መንቀሳቀሳቸውን አቁመው ክንፎቻቸውን ዝቅ እንዳደረጉ፣ ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ድምፅ ተሰማ።

26. ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ የሰንፔር ዙፋን የሚመስል ነገር ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የሰው መልክ የሚመስል ነበር።

27. ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ በእሳት መካከል እንዳለ የጋለ ብረት፣ ከወገቡም በታች እሳት ይመስል እንደነበር አየሁ፤ ደማቅ ብርሃንም በዙሪያው ነበር።

28. በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደሚታየው ቀስተ ደመና በዙሪያው ያለው ጸዳል እንዲሁ ነበር።ይህም የእግዚአብሔር ክብር መልክ አምሳያ ነበረ። ባየሁትም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ፤ የአንድ ተናጋሪን ድምፅ ሰማሁ።

ሕዝቅኤል 1