ሕዝቅኤል 1:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በሠላሳኛው ዓመት፣ በአራተኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን፣ በኮቦር ወንዝ አጠገብ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ራእይ አየሁ።

2. ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ቀን፣

3. በባቢሎናውያን ምድር በኮቦር ወንዝ አጠገብ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቡዝ ልጅ፣ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ፤ በዚያ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረች።

4. እኔም አየሁ፤ ስመለከትም፣ እነሆ ዐውሎ ነፋስ ከሰሜን በኩል መጣ፤ ይኸውም በታላቅ ብርሃን የተከበበ፣ መብረቅን የሚረጭ ታላቅ ደመና ነበረ፤ የእሳቱም መኻል የጋለ ብረት ይመስል ነበር።

5. በእሳቱም ውስጥ የአራት ሕያዋን ፍጡራን አምሳያ ነበረ፤ መልካቸውም የሰው ቅርጽ ይመስል ነበር።

6. እያንዳንዳቸውም አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበራቸው።

7. እግራቸው ቀጥ ያለ ነበር፤ ኮቴያቸውም እንደ ጥጃ ኮቴ ያለ ሲሆን፣ እንደ ተወለወለ ናስም ያበለጨልጭ ነበር።

8. በአራቱ ጐኖቻቸው ባሉት ክንፎቻቸው ሥር የሰው እጅ ነበራቸው። አራቱም ፊቶችና ክንፎች ነበሯቸው፤

9. ክንፎቻቸውም እርስ በርስ ይነካኩ ነበር። እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ ወደ ኋላቸውም ዞር ብለው አይመለከቱም ነበር።

10. ፊታቸውም እንዲህ ነበር፤ አራቱም እያንዳንዳቸው የሰው ፊት ነበራቸው፤ በቀኝ በኩል የአንበሳ ፊት፣ በግራ በኩልም የበሬ ፊት ነበራቸው፤ እያንዳንዳቸውም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።

11. እንግዲህ ፊታቸው ይህን ይመስል ነበር፤ ክንፋቸውም ወደ ላይ ተዘርግቶ ነበር፤ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ክንፍ ነበራቸው፤ የእያንዳንዱም ክንፍ የሌላውን ክንፍ ይነካ ነበር፤ ሁለቱ ክንፎቻቸው ሰውነታቸውን ይሸፍኑ ነበር።

12. እያንዳንዱ ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሄድ ነበር፤ ወደ ኋላም ሳይዞር መንፈስ ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄድ ነበር።

ሕዝቅኤል 1